Newsletter Signup

Sign-up to stay in touch with Saint George FC

Reagent/Protectorator
Yidnekatchew Tessema
Mengistu Worku

St. George Gallery

የ80ኛው አመት ክብረ በአል ማክበሪያ ሎጎ በነገው ዕለት በይፋ ይመረቃል

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የተመሰረተበት 80ኛ አመት ክብረ በአል በመጪው አመት 2008ዓ.ም. በደመቀ እና ባሸበረቀ ሁኔታ ይከበራል፡፡ የዚሁ ክብረ በአል አካል የሆነው እና የ80ኛ አመት ክብረ በአሉ ሎጎ በነገው ዕለት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፅህፈት ቤት በሚካሄድ ደማቅ ስነ ስርአት ይመረቃል፡፡

ሎጎው በአሉን ለማክበር ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች አንዱ የሆነው የሲምፖዚየም እና መፅሄት ዝግጅት ኮሚቴ ባወጣው የሎጎ ውድድር መወዳደሪያ ማስታወቂያ መሰረት ለውድድር ከቀረቡት አስራ ሶስት ሎጎዎች ውስጥ ነጥረው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ ስራዎች ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በዚህም መሰረት አንደኛ በመውጣት የ80ኛ አመት ማክበሪያ ሎጎ በመሆን የተመረጠውን ሎጎ በመስራት ውድድሩን ያሸነፈውና የ10000 ብር ተሸላሚ የሆነው አቶ ቴዎድሮስ ግደይ ሲሆን ሁለተኛ የወጣውን ሎጎ በመስራት የ7500 ብር ተሸላሚ የሆነችው ነፃነት ሬጋን ናት፡፡ የሎጎ ውድድሩን አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው አቶ ቴዎድሮስ ውድድሩን በማሸነፉ የተሰማው ደስታ ልዩ መሆኑን ገልፆ በተለይም ሰፊ ታሪክ ባለው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሰማንያኛ አመት ክብረ በአል ሎጎን በመስራቱና በማሸነፉ ትልቅ ክብር እንደተሰማው ገልጿል፡፡ የሎጎ ዲዛይን ውድድሩን በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው ነፃነት ሬጋንም ደስታዋን በሚከተለው መልኩ ገልፃለች፡፡ «ይህንን ውድድር ማሸነፌ በተለይም ለዕኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ እዚህ ክለብ ባልጫወትም ከልጅነቴ ጀምሮ እየደገፍኩ ያደግኩት ይህንኑ ክለብ ነው፡፡ስለዚህም በዚህ ታሪካዊ በአል ላይ አሸናፊ ሆኜ መገኘቴ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ወደ ፊትም ይህንን በአል የሚያደምቁና የእኔን ሙያ የሚመለከቱ ማናቸውንም ነገሮች በነፃ ለመስራት ቃል እገባለሁ፡፡ ደጋፊውም የክለባችንን የ80ኛ አመት ክብረ በአል ደማቅ እና አይረሴ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በየሙያው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እጠይቃለሁ» በማለት የ80ኛ አመት የምስረታ በአል የሎጎ ውድድሩን በማሸነፏ  የተሰማትን ደስታ ገልፃለች፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የ80ኛ አመት ክብረ በአል አዘጋጅ አቢይ ኮሚቴ እና የሲምፖዚየም እና መፅኄት ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ልኡልሰገድ ረታ በበኩላቸው ውድድሩ ለአወዳዳሪዎቹ እጅግ በጣም አሰደሳች እንደነበርና የሎጎ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ስራዎች በመቅረባቸው አሸናፊውን ለመምረጥ  አሰቸጋሪ እንደነበር ገልፀው በውድድሩ የተሳተፉትን እና አሸናፊዎችን ስለተሳትፏቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አሸናፊው ሎጎ በነገው ዕለት በቅሎ ቤት በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፅህፈት ቤት የ80ኛ አመት ክበረ በአል አቢይ ኮሚቴ፤ የሲምፖዚየም እና መፅሄት አዘጋጅ ኮሚቴዎች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት የሚመረቅ ይሆናል፡፡