
የአትሌቱ አጭር የህይወት ታሪከ
አትሌት ደምሰው ጸጋ በቀድሞ ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ልዩ ስሙ ጦሴ ቀበሌ ከአባቱ ከአቶ ጸጋ አበበ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ዘነቡ ዘለቀ መጋቢት 6 ቀን 1980 ዓ.ም ተወለደ፡፡
እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በተወለደበት ቀበሌ በጫጫ ከተማ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ በውስጡ ባደረበት ከፍተኛ የስፖርት ፍላጎት በትምህርት ቤቶች የሩጫ ውድድድር መካፈል ጀመረ፡፡
በተሳተፈባቸው የሩጫ ውድድሮች ላይ ባስመዘገባቸው ውጤቶች ወረዳውን በመወከል ከነበሩት ተወዳዳሪዎች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞንን በመወከል አዲስ አበባ ላይ በተዘጋጀው ውድድር ላይ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በአትሌቲክስ ቡድን ውስጥ በመታቀፍ በ5 ሺ እና በ10ሺ ሜትሮች እንዲሁም በአዲስ አበባ የክለቦች ሻምፒዮና እና በኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ተካፍሎ ልዩ ልዩ ሜዳሊያዎችን ተሸልሟል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአትሌቲክስ ስፖርት ከ8 ዋንጫዎች በላይ ሲያገኝ የደምሰው ድርሻ የጐላ ነበር፡፡
አትሌት ደምሰው እናት አገሩን በመወከልም በአገር አቋራጭ ውድድሮችና በተለያዩ አገራት በተዘጋጁ የአለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው አትሌቱ ባደረበት ድንገተኛ ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ32 አመቱ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም እዛው አሜሪካ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡አትሌት ደምሰው ጸጋ አንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር፡፡የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በአትሌቱ ህልፈተ ህይወት ተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡